"የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ መናድ ሚድያዎቻችን የጥፋት መሳርያ እንዲሆኑ አድርጎዋቸዋል"

ወይዘሮ ሊያ ካሳ፡ የትግራይ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ
----------------------
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አዘጋጅነት በመቐለ ከተማ ሚድያዎቻችን በህዝቦች እይታ ምን እንደሚመስሉ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

መድረኩ በንግግር የከፈቱት የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊያ ሲሆኑ በንግግራቸው የሀገራችን ሚድያዎች ሀገራችን ባለፉት 28 ዓመታት ላስመዘገበችው የልማት ድል የራሳቸው የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ጠቁመዋል።

ይሁንና ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ችግር አመካኝነት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰቦች እና መርሆች እየተመቱ ሚድያዎቻችን የትምክህተኛ ቡድን መፈንጫ መድረኮች ወደ መሆን መሸጋገራቸው ገልጸዋል።

ህዝቦች ራስ በራሳቸው እንዲጠራጠሩ፣ ወደ ግጭት እና ማንነትን መሰረት ወደሆኑ ግጭቶች እንድያመሩ በማድረግ በኩል ሚድያዎች ታሪክ የማይረሳው ጥፋት ማጥፋታቸው ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት "እንደ እነ ኢሳት ያሉ ሚድያዎች በህዝቦች ዘንድ የዘር ማጥፋት አዋጅ አውጀዋል" ብለዋል።

"ህዝቦች ላባቸው አንጠፍጥፈው ያፈሩትን ሀብት እየተዘረፈ እና ከቀያቸው እየተባረሩ የሀገራችን ሚድያዎች ሀይ ባይ አጥተው ጉዳዩን ሲያጋግሉት ነበር" ያሉት ሀላፊዋ በተለይም ኢቢሲ፣ ፋና እና ዋልታ "በታሪክም በህግም ተጠያቂ ናቸው" ብለዋቸዋል። ወይዘሮ ሊያ ይሄንን ያሉበት ምክንያት ሲያስቀምጡ ህዝብን ሊያስጨርስ የሚችል ዶክመንተሪ ተዘጋጅቶ በተመሳሳይ ሰዐት ለህዝብ ቀርበዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆደ ሰፊነት ነው እንጂ ዶክመንተሪው በአንድ ሰዐት የዘር ጭፍጨፋ የምያስከትል መሆኑ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የምክክር መድረኩ አሁን ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለ ሲሆን በዛሬው ዕለት ሁለት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይውላል።