ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ሃሳብ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ሉዓላዊ መብት የሚጋፋ ነው

መስከረም 15/2012 ግብጽ በአባይ ወንዝና በህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ሃሳብ የኢትዮጵያን በወንዙ የመጠቀም ተፈጥሯዊና ሉዓላዊ መብቷን የሚጋፋ መሆኑን በናይል ትብብር መድረክ የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የናይልን ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በጋራ ለመጠቀም እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር መስከረም 2015 በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም አስር አንቀፅ ያለው የመርሆዎች ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

ይሄንን ተከትሎም ከሶስቱም ሀገራት የተውጣጡ 15 የባለሙያዎች ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተው የደረሱበትን ውጤት ለውሃ ሚኒስትሮቻቸው አቅርበዋል።

የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮችም መስከረም 2018 በአዲስ አበባ ለመወያየት ከተገናኙ በኋላ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ ቃለ ጉባኤውን ሳይፈርሙ ቀርተዋል።

የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ግብጽ ያቀረበችው ሃሳብ ሶስቱ ሃገራት ከፈረሙት የስምምነት መርሆዎች ያፈነገጠ ነው።

ግብጽ ያቀረበችው የእቅድ ሃሳብ ወይም ፕሮፖዛል “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት ራስ ወዳድነት የተንጸባረቀበትና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብቷን የነፈገ ነውም ብለዋል።
ኢዜአ